Friday, February 5, 2010

Neg Bene (ewnetu Tekeste)

ጥር ፲፰ ቀን ሺህ .

ነግ በኔ

ከእውነቱ ተስተ

ብእሬ በሰሞኑ ወደ ተከሰተው አሰቃቂና አሳዛኝ ወደ ሆነው የሔይቲ ሕዝቦች እልቂት እንድታተኩር ሰብአዊ ሕሊናዬ አስገደደኝ፡፡

ይህ የምንኖርበት ዓለም አስደናቂም ሆነ በከፍተኛ ሁኔታ አሰቃቂ ክስተቶች የሚታዩበት የእልቂትና የጥፋት ዓለም በመሆኑ ወራቶችና ዓመታት በተለዋወጡ ቁጥር የምንሰማውና የምናየው አሳዛኝ ሁኔታ መፈጠራችንን እስኪያስጠላን የደረሰ ዘግናኝና ድንገተኛ ነገር ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡

እግዚአብሔር ሰውን ማለትም አዳምንና ሔዋንን በአምሳሉና በመልኩ እንደፈጠራቸውና በኤዶም ገነት እንዳኖራቸው በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ. እና ባለው ተጠቅሷል፡፡

ምንም እንኳን አዳም የፈጣሪውን ትእዛዝ ቢሽርም ቅሉ እግዚአብሔር ፈቅዶ ፈጥሮታልና አንዲያ ልጁን ልኮ የአዳምን ሞት ሞቶ በሞቱ ዲያብሎስን ድል ነስቶ ይቅር ብሎት ከሞት ሞት አድኖ ወደ ቀድሞ ቦታው መልሶታል፡፡

ሰው ግን እግዚአብሔር የዋለለትን ከባድ ውለታ በመርሳት ትእዛዙን እየሻረ አሁንም ወደ ሁለተኛው ሞት ለመሔድ ሲጣደፍ ይታያል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወን. ምዕ. ፲፭ . ፲፪ እና ፲፫ ባለው እኔ እንደወደድካችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም ይላል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ገላትያ ሰዎች በላከው መልእክቱ ምዕ. ፳፰ እና ፳፱ ላይ አይሁዳዊ’ የግሪክ ሰው’ ባርያ’ ጨዋ’ ሴት’ ወንድ’ የለም አንድ ናችሁ ብሎናል፡፡ አዎን መጀመሪያ የተፈጠረው የአዳም ዝርያዎች መሆናችን የሚካድ አይደለም፡፡ ቅድሱ የእግዚአብሔር ቃል ‘’ቅሩብ እግዚአብሔር ለየዋሐነ ልብ’’ ልባቸው ንጹህ ለሆነ የዋሆች እግዚአብሔር ቅርባቸው ነው እንዳለው እግዚአብሔር የተትረፈረፈው ሐብታምና ባለጸጋ ነውና በአንድነትና በፍቅር ለለመነው ሁሉ የለመኑትን የማይነሳ የነገሩትን የማይረሳ ይቅር ባይ አምላክ በመሆኑ ቃሉ እንዳለው በአንድ አካልነታችን አምነን ፈጣሪያችንን መማጸኑ ይበጀናል፡፡

ትንቢተ ዮናስን የተመለከትነው እንደሆነ ነቢዩ ዮናስ ወደ ነነዌ ከተማ ገብቶ በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች በማለት እየጮኸ የእግዚአብሔርን ቃል ሲያስተላልፍ የነነዌ ንጉሥ አዋጅ አሳውጆ ማቅ ለብሶ ትእዛዙን በጥብቅ አስተላልፎ የነነዌ ሰዎች በከባድ ፆምና ጸሎት ተወስነው ከክፉ መንገዳቸው በመመለስ ወደ እግዚአብሔር በማልቀሳቸውና ከልብ በማዘናቸው እግዚአብሔር ይቅር ብሏቸው መቅሰፍቱ ሊወገድላቸው ችሏል፡፡

እኛስ ወደ ራሳችን መለስ ብለን ተመልክተናል? ራሳችንንስ መርምረናል? ከስህተታችንና ከአጢአታችን በንስሐ ለመመለስ ጥረት እያደረግን ነውን? ‘’ነግ በኔ’’ ነውና እኛ ማንና ምን እንደሆን ተረድተን ከዚህ ዓለም ዝባዝንኬ ኃጢአት ተወግደን መልካም ሥራ ለመሥራት እንጣደፍ፡ ወደ መጥፎ ተግባራት መሮጥ ብናቋርጥና ወደ እግዚአብሔር ቤት ብንመለስ መልካም ነው እላለሁ፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በላከው መልእክቱ ምዕ. ፲፰ ላይ ‘’ነገር ግን ከናንተ ዘንድ በምኖርበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ በመልካም ነገር ተፈላጊ ብትሆኑ መልካም ነው’’ ብሏልና እግዚአብሔር የሚወደውን ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

ፍሬ ጉዳዩ በዚህ ባለፉት ሳምንታት በዜና ማሰራጫዎች የምንሰማውና የምናየው በጣም አሰቃቂ የሆነው የሔይቲ ከተማ መንቀጥቀጥና ከባድ የሕዝብ እልቂት ጉዳይ ሲሆን የአሜሪካ መንግሥት ያደረገው የተቀደሰና ርኅራኄ የተሞላበት አፈጻጸም ተመልካችን ያስደሰተና የሳበ እግዚአብሔር የሚወደው የተቀደሰ ተግባር ነው፡፡

የእነኚህ ወገኖቻቺን እልቂት የሚመለከተው የአሜሪካንን መንግሥት ብቻ ሳይሆን ‘’ነግ በኔ’’ ብለን የምናስበውን የዓለም ሕዝቦች ስለሆነ ማንኛውም ሰው እጁን እንዲዘረጋ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

የማቴዎስ ወን. ምዕ. ብንመለከተው ‘’የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው መጽናናትን ያገኛሉና’’ ይላል፡ ለእነኚህ ወገኖቻቺን የደረሰባቸውን ጉዳትና ስቃይ አስበን ብናዝንላቸው አጸፋውን ደስታ እናገኛለን፡፡

ቢሆንም በደረቁ ሐዘን ብቻ አይጠቅማቸውም፡፡ ‘’ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ችግር ለደረሰበት ወንድማችሁ ለችግሩ የሚያስፈልገውን ካልሰጣችሁት ሒድ እሳት ሙቅ ብትሉት ምን ይጠቅመዋል ብሏልና ሐዘናችን እጃችንን ከመዘርጋት ጋር መሆን አለበት፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ምዕ. .፲፯ አብረን እንድንከብር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን ይላል፡፡

ምንም እንኳን በስፍራው ተገኝተን አብረን ችግራቸውን ለመካፈል ባንችል በያለንበት ሆነን ይህን እንደ ራኄል እንባ የሚያነባውን ድንጋይ ተጭኖት የሚያነሳለት ያጣውን ወገናችንን አቅማችን በፈቀደ መጠን እጃችንን ብንዘረጋለት ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር ፼፲፩ . ላይ ‘’በተነ ለችግረኞችም ሰጠ ጽድቁም ለዘለዓለም ይኖራል’’ ያለውን ጸጋ ከፈጣሪያችን በእጥፍ እንደምናገኝ የተረጋገጠ ነው፡፡በመጽሐፈ ጦቢትም ምዕ. . ደግሞ ከገንዘብህ ከሐብትህ ምጽዋትን ስጥ ምጽዋትም በመጸወትህ ጊዜ በገንዘብሕ አትዘን ከደሀም ፊትህን አትመልስ እግዚአብሔርም ገጸ በረከቱን ከአንተ አይመልስም ይላል፡፡

እግዚአብሔር በጥበቡ የሠራው ታላቅ ሕንፃ ድንጋይ ተንዶበት ሲፈርስ ‘’ነግ በኔ’’ ብለን ታላቅ ሐዘን ተሰምቶን አሁኑኑ በላይኛው ቤት የማይፈርስ ዘለዓለማዊ የሆነ መዝገብ መሰብሰብና የማይናድ ሕንፃ ማነጽ ይገባናል፡፡

ከእነዚህ በድንጋይ ከተጨፈለቁት ተርፈው የሚገኙት በሞትና ሽረት ላይ ያሉት ወንዱና ሴቷ ሕፃን ሽማግሌው የደም እንባ ሲያነቡ በበኩላችንም ጠብታ እንባ አንንፈጋቸው፡ ወገን እባካችሁን ጩኸቱና ዋይታው በዓለም ዙሪያ እያስተጋባ ስለ ሆነ አብረን ወደ ፈጣሪያችን እንጩህ ‘’ነግ በኔ’’ ነውና፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በላከው ፪ኛ መልእክቱ ምዕ. . ‘’እንግዲህ እግዚአብሔር በኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን’’ ይላል፡፡

ስለዚህ በየቤተክርስቲያኑና በየኮሚኒቲው ያላችሁት አባቶች ብፁዐን ጳጳሳት ቅዱሳን መነኮሳት ክቡራን ካህናትና ፓስተሮች ምህላችሁንና ጩኸታችሁን ወደ ፈጣሪያችሁ በማሰማት ማንኛውም ሰው ‘’ነግ በኔ’’ እያለ ለተጎዱት ወገኖች የማይታጠፍ እጁን ከመዘርጋት እንዳያቋርጥ ሐዋርያዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እያሳሰብኩ ከራሳችሁ በመጀመር በተቻለ መጠን አስተዋጽኦው እንዲቀጥል ሕዝቡን እንድትቀሰቅሱትና በየበኩሉ መሥዋዕትነትን እንዲከፍል እንድታደርጉ ይቅር ባይ በሆነው በሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ስም እጠይቃለሁ፡፡

የተቀደሱት አባቶቻችን ለችግረኞች እጅ እንዲዘረጋ በሚጠይቁበት ጊዜ ሁሉ የቅድመ አያቶቻቸውን ዘይቤ ‘’ሃምሳ ሎሚ ለሃምሳ ሰው ጌጡ ነው ለአንድ ሰው ሸክሙ ነው’’ የሚለውን ይጠቅሳሉ በዚህ መሠረት የተቻላችሁን እየሰነዘራችሁ ወገን እባካችሁ የተጫነብንን ድንጋይ አንሱልን እያሉ የሚጮሁትን ወገኖቻቺንን ጊዜ ሳንሰጠው የአንድ ቀን ቁርስ’ ምሳ" እና እራት ምግባችንን ዋጋ እንኳ ቢሆን አስበን በመለገስ ልባችንን ከጎናቸው ሳናርቅ ልቅሶና ጩኸታቸውን እንድንረዳቸው በድንጋይ ተጨፍልቀው ባለቁት ሕዝቦች ስም እማፀናለሁ፡፡

ይቅርታውና ምሕረቱ ምን ጊዜም ቢሆን የማይጓደለው መሐሪ አምላካቺን ምሕላችንንና የወገኖቻቺንን ልቅሶ ሰምቶ በምሕረት ዓይኑ እንዲመለከታቸው መልካም ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

አሜን