Tuesday, January 12, 2010

Tikimu Min Yihon (ከእዉነቱ ተከስተ)

ጥቅምት ፲፮ ቀን ፪ ሺህ ፪ ዓም
ጥቅሙ ምን ይሆን?
እዉነቱ ተከስተ እባላለሁ ብእሬ መንቀሳቀሷን ካቋረጠች ዘመናት ኣሳልፋለች ፡፡ በውዲቷ ሐገሬ በነበርኩበት ጊዜ ብእሬን እንዳታንቀላፋ የሚቀሰቅሷት ኣቢይ ጉዳዮች ስለሚከሰቱ ወቅቱን ጠብቃ ከመንቀሳቀስ ችላ ያለችበት ጊዜ ኣልነበረም ፡፡የቅዱሳን ኣባቶቻቺን ኣምላክ ክብር ምስጋና ይግባውና በጸሎታቸው ተጠብቄ እድል በማግኘቴ ወደ ኣሜሪካ ከመጣሁ ጥቂት ዘመናትን ቆጥሬኣለሁ ፡፡
ቢሆንም የነበርኩበት ኣካባቢ ለቅዱስ ሥራና ለኣንድነት ለሰላምና ለፍቅር የሚሯሯጥ ሕዝብ የሚበዛበት ስለነበር ድካም የተሰማትን ብእሬን እረፍት ኣልነሳኋትም ፡፡እንደ ኣጋጣሚ ኣካባቢውን ለመቀየር ፈልጌ ካንሳስ ከመጣሁ ዋል ኣደር ብሏል ፡፡ የኣገሩ ኑሮ ፋታ የማይሰጥና የሚያሯሩጥ በመሆኑ ከብዙ ሰው የምገናኝበትና ብእሬን የማንቀሳቅስበት ጊዜ ኣላገኘሁም ፡፡ በምትተርፈኝ ትንሽ የእረፍት ጊዜዬ ኮምፒውተሬን ከመጎርጎር ኣልተቆጠብኩም ፡ በጊዜው የሚነፍሱ ወሬዎችም ኣላመለጡኝም ፡፡ሆኖም ብእሬን እንዳንቀሳቅስ የገፋፋኝ ኣቢይ ጉዳይ ኣልተከሰተልኝም ነበር ፡፡
የምኖረው ከከተማ ዳር ሆኖ ሳለ እንደ ኣጋጣሚ ከኣንድ የጥንት ጓደኛዬ ጋር በመገናኘት ወደ ካንሳስ መጥተን ከደብረሣሕል መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የተጻፈ ማስታወቂያ ተለጥፎ ኣይቼ ካነበብኩት በኋላ ጉዳዩ ምን ይሆን በማለት በተወሰነው ሰኣት በስብሰባውላይ ተገኘሁ ፡፡
በወቅቱ ባየሁት የስብሰባ ትርኢት ተገርሜ ሳለሁ ችላ ብዬ ኣሳልፌው የነበረውን ጓደኛዬ የስብሰባውን ጉዳይ የሚመለከት በኢንተርኔት ወጥቷልና በ WWW ETHIO MEDIA .COM QUETERO የሚለውን ኣውጥተሕ ተመልከት ብሎ ስልክ ደውሎልኝ ነሐሴ ፲፰ ቀን ፪ ሺህ ፩ ዓም እና August 15/ 2009 ዓም ከቄስ ኣስተርኣየና ከደብረ ሣሕል መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የተጻፈውን ኣስር ገጽ ጽሁፍ ስመለከተው በጣሙን ኣዘንኩ ፡፡
ኣንድ ተራ ቄስ እግዚኣብሔር ኣክብሮ የሾማቸውን ጳጳስ ኣጭበርባሪ ብሎ መስደብና በኢንተርኔት ማውጣት እግዚኣብሔር የሚወደውና ከኣንድ ቄስ የሚጠበቅ ኣይደለም ፡ እንዲያውም በተመልካቹ ዘንድ ያላዋቂነታቸው መመዘኛ ሆኗል ፡፡ እንደተረዳሁት እኒህ ኣባት ከሰዳቢው ቄስ በላይ እውቀት ያላቸው በመሆናቸው እንደ ቅዱሳን ኣባቶቻቸው ስድቡን በጸጋ የተቀበሉት ቢሆንም ቅሉ የሁለቱን ሁኔታ ሳመዛዝነው ኣጸፋውን ስድብ ለመመለስ የሚሳናቸው ኣይደሉም ፡፡
ኣንዳንድ ሰው ራሱ የሚፈጽመው ከባድ ስህተት ለራሱ ሳይከሰትለትና ይፋ ሳይወጣበት ሲቀር ሰውን በመስደብ በኣሽሙርና ስም በማጥፋት እውነተኛና ኣዋቂ ለመባል ሌላውን የጎዳና የረካ ይመስለዋል፡፡ ጥቅሙ ምን ይሆን ? ይህ የስድብ ጋጋታ ጳጳሱ ካገዷቸው በኋላ የተከሰተ ቂም መቅረፊያ መሆኑን ማንም ይረዳዋል ፡፡ምናለ ? በስድቡ ምትክ ሰውን በመንፈሳዊ ሕይወት የሚገነባ ትምህርትና የእግዚኣብሔር ቃል ተክተው ቢያቀርቡ ? በጣም ያሳዝናል ፡፡
በመሰረቱ በኢንተርኔት የወጣው August 15 / 2009 የተጻፈው ጽሁፍ እንደሚገልጸው በጥንተ ኣብሶ ምክንያት በተነሳው ውዝግብ ካህናችን ታገዱ የተወሰነውም ውሳኔ እንዲታረም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያሬክ ለቅዱስ ሲኖዶስና ለሊቃውንት ጉባኤ በመጻፍ ደግመን በማስረዳት ለኣምስት ዓመታት መፍትሄ ስንጠባበቅ ቆየን የሚመለከተው ክፍል ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ መልስ ሳይሰጥበት ቆይቷል ይላል ፡፡ ለመሆኑ እንደ ጽሁፉ ኣባባል ቄሱ የጳጳሱን እግድ ‘’ግዝት’’ ኣክብረው ኣምስት ዓመት ሙሉ ሳያገለግሉ ቆይተዋልን ? ወይስ በንቀት እግዱን ሽረው ኣገልግለዋል ? መልሱን ቀጥለን ከጽሁፉ እንረዳለን ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ የታወቁና በቂ ችሎታ ያላቸው የሚደነቁ ሊቃውንቶች እንዲሁም ጳጳሳት እንዳሉት ለማንም የተሰወረ ኣይደለም መልስ ለመስጠትም ያለ ምክንያት ጆሮ ዳባ ልበስ የሚሉ ኣይደሉም ፡፡ እንደተረዳሁት ዋናው ምክንያት የደብረሣሕል መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክህነትና ሲኖዶስ ወይም በኣሜሪካ ባለው ሲኖዶስ ስር ባለመሆኗ ጥያቄውን ሁሉ ለማሟላት እናንተ ማን ናችሁ የሚለው ኣጠያያቂ ጉዳይ ሲነሳ ኣፍራሽ ስለሚሆን በቅድሚያ እንደ ማንኛዉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኣብያተ ክርስቲያናት ኣቋማችሁን ወደ ኣንደኛው ወገን ማስተካከል የሚገባ ይመስለኛል ፡፡ ይህ ካልተሟላ ለጥያቄው መልስ ሰጪ ለማግኘት ያዳግታል ፡፡
ቄሳችን ታገዱ ለተባለው ጳጳሱ ስህተቱን ተገንዝበው በምእመናኑ በኩል ችግር እንዳይፈጠር ቄሱን የማገድ ሥልጣናቸው የሚፈቅድላቸው ለመሆኑ ከማንም የሚሰወር ኣይደለም ፡፡ ሆኖም እግዱ ተነስቷል የተባለበትን ቃለ ጉባኤ ጓደኛዬ ኣምጥቶልኝ ስመለከተው የታገዱት ቄስ ኣስተርኣየ በኣባልነት ተቀምጠውና ተመዝግበው በመገኘት በራሳቸው ጉዳይ ውሳኔ የሰጡበት ኣንድም ጳጳስ በኣባልነት ያልተመዘገበበትና ያልፈረመበት የካህናት ስብስብ ጉባኤ መሆኑን ተመለከትኩት ቄሱም ከታገዱበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ከማገልገል ያላቋረጡ መሆኑንም ተረዳሁ ፡፡
ኣንድ ጳጳስ ያገደውን እንኳንስ የታገዱት ቄስ በኣባልነት ተገኝተው የፈረሙበት የካህናት ስብስብ ጉባኤ ይቅርና ጳጳሳት እንኳን በኣባልነት ቢናሩበት እግዱን ማንሳት ፈጽሞ ኣይችሉም ፡፡ የካህናቱም ጉባኤ በውሳኔው ላይ እግዱን ኣንስተናል ኣላለም ፡፡ በትክክል ሲታይ ቄሱ ይህን ምክንያት ኣድርገው እግዱ ተሽሮልኛል በማለት ሕዝቡ ሳያውቅ በስውር የጳጳሱን እግድ በስልጣናቸው ሽረው ኣገልግሎት ሳያቋርጡ መቀጠላቸው ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሕግ ውጭ ስለሆነ በከባድ ሁኔታ እንደሚያስጠይቃቸው ጥርጥር የለውም ፡፡ በእርሳቸውም ስር ሆኖ የሚገለገለው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኣማኝ መታገዳቸውን እያወቀ የተገለገለ ከሆነ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሕግና ሥርአት ኣፍርሷል ማለት ነው ፡፡ ኣሁንም ቢሆን ይህን ያልተረዳ ቢኖር ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግና ኣሉ ከሚባሉት ከሁለቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስ ውሳኔ እስኪሰጥበት ድረስ በታገዱት ቄስ ከመገልገል መቆጠብ ያስፈልጋል ፡፡
ወደ መጀመሪያው ነጥብ ልመለስና ከላይ በመግቢያው እንደጠቀስኩት ቅዳሜ ነሐሴ ፱ቀን ፪ ሺህ ፩ ዓም ከ፪ ሰዓት PM ጀምሮ ስለ እመቦታችን ማርያም ጉዳይ በግብጹ ጳጳስ በኣቡነ መቃርዮስ ማብራሪያ ይሰጣልና በግብጽ ቤተ ክርስቲያን እንድትገኙ የሚል ማስታወቂያ በደብረ ሣህል መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በኩል ወጥቶ ኣይቼ ምንም እንግዳ ብሆን ቅሉ እስቲ ምን እንደሚባል ልስማ በማለት በተወሰነው ሰዓት መገኘቴንና ከላይ መጥቀሴን ኣስታውሳለሁ ፡፡ የስብሰባውን ሁኔታ ስመለከት በጊዜው የነበረው ሕዝብ ብዛት በግምት ከሀያ ኣምስት ኣይበልጥም ነበር ፡፡
ጳጳሱ ኣቡነ መቃርዮስ ትምህርት ለመስጠት ይመስላል በኣውደ ምሕረቱ ቆመው ተናግረው ሲያበቁ ከተቀመጡ በኋላ ጥያቄኣችሁን በጽሁፍ ኣምጡ በማለት ኣዘው ስለ እመቤታችን ማርያም ጉዳይ ንግግር ጀመሩ ፡፡ ሆኖም የሚደረገው ነፃና ግልጽ ውይይት መስሎኝ ነበር ታዲያ በማስታወቂያው ላይ ጥያቄና መልሶቻችሁን በጽሁፍ ኣምጡ ኣልተባለም በጽሁፍ መስጠትን ምን ኣመጣው ? የሚል ኣስተሳሰብ በጆሮዬ ኣቃጨለብኝ ፡፡
ኣፈጻጸሙን ኣተኩሬ ስመለከት ጠያቂዋች በብጣቂ ወረቀት ጽፈው የሰጡት ጥያቄ ባለቤቱ በቃል ኣብራርቶ ቢገልጸው ኣገላለጹን የሰማውም መልስና ኣስተያየት ሰጥቶበት ከፍተኛ ትምህርትና እውነተኛ መልስ እንደሚያገኝ ኣልጠራጠርም ነበር ፡፡ ለጳጳሱ የተሰጡት ብጣቂ ወረቀቶች ከፊታቸው ተከማችተው በጳጳሱ ሲነበቡ ትክክለኛ ንባቡ ለጉባዔው የተገለጸው ከሞላ ጎደል ከመሆኑም በላይ ኣንዳንዶቹም ተመሰቃቅለው ሳይነበቡ የቀሩ ኣይታጡም ፡፡
በዚህ ላይ ኣንድ ኣዛውንት በቃላቸው ሊጠይቁና ሊያስረዱ እጅ ኣውጥተው ፈቃድ ሲጠይቁ ጳጳሱ ኣይቻልም ! ቁጭ በል ! ጥያቄህን በጽሁፍ ኣቅርብ ብለው ስለከለከሏቸው በቂ ወረቀትና መጻፊያ እንኳን የያዙ ኣልመሰለኝም ብቻ በተቻላቸው መጠን ጽፈው ያቀረቡ ሲሆን ጽሁፍ የማይችሉት እናቶችና ሌሎችም ታግደው ምንም ኣስተያየት ሳይሰጡና ጠይቀው ሳይረዱ ታፍነው ቀርተዋል ፡፡ የጠቀስኳቸው ኣባት ያቀረቡት ጥያቄ እንዲህ የሚል ነበር ፡
፩ኛ በተኣምረ ማርያሟ ላይ እመቤታችን በኣምላክ ልቦና ታስባ ትኖር ነበር ይላል ፡
፪ኛ በመዝሙር 131 ላይ ደግሞ እግዚኣብሔር ማደሪያው ትሆን ዘንድ ወዿታልና ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ነች ብሏታል ፡፡
፫ኛ በቅዳሴ ማርያም መጽሐፍ በቁጥር 38 ላይ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐናና ከኢያቄም የተወለድሽ እንጂ በኃጢኣት ፍትወት የተጸነሽ ኣይደለሽም ይላታል ፡፡ ይህ ቃል በኃጢኣት እንዳልተፀነሰች ይገልጻል ፡፡
፬ኛ ያለፉት ቅዱሳን ኣባቶች በኣርብ ውዳሴ ኣምላክ ላይ በሰው ሁሉ የደረሰ የኣዳም ኃጢኣት ስንኳ ኣልደረሰብሽም ብለዋታል ፡፡ ታዲያ ይህን የመሳሰለው በምን መልኩ ይታያል? በማለት በጥያቄኣቸው ላይ ከዘረዘሩ በኋላ በእግዚኣብሔር ልቦና ታስባ የምትኖር ስለነበረና ማደሪያው ልትሆን የመረጣትን ቅድስት እናቱን ኣዳም ከፈጸመው ኃጢኣት ገና ከህፃንነቷ ጀምሮ ለማንፃት ምን ይሳነዋል ? በዚህ ሁኔታ እመቤታችን ማርያምን ከኃጢኣት ኣንጽቷታል ቢባል እንዴት ካቶሊክ ያሰኛል ? የተዋሕዶንስ መሰረት እንዴት ያፋልሳል ?
፭ኛ የኢትዮጵያ ሊቃውንት በተረጎሙትና በጻፉት የወንጌሉ ኣንድምታ የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፴፭ ላይ ‘’ወኣውሥኣ መልኣክ ወይቤላ መንፈሰ እግዚኣብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል “ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ” ኃይለ ልዑል ወልድ ሥጋሽን ይለብሳል ፡፡ ኣንድም መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል ኃይለ ልዑል ወልድ ከሦስቱ ግብራት ይከለክልሻል ይላል እንጂ ከኣለብሽ የኣዳም ውርስ ኃጢኣት ያነጻሻል የሚል ኣልተጻፈም ፡፡
በኣጠቃላይ እመቤታችን ጌታችን ኢየሱስን እስክትፀንስ 15 ዓመት የኣዳምን ኃጢኣት ተሸክማ ኖረች የምንለው ምን ማረጋገጫ ይዘን ነው ? ኃጢኣተኛ ነች የምንለውስ ምን ለማግኘት ፈልገን ነው ? ጥቅሙስ ምን ይሆን ? ያቀረብኳቸው ጥያቄዋች ቢብራሩና ኣስተማማኝ ማስረጃ ቢጠቀስልኝ መልካም ነበር ፡፡እኔ ግን ጉዳቱ እንጂ ጥቅሙ ኣይታየኝም ምእመናኑን ሰላም መንሳት ነው ፡ ሲሉ ላቀረቡት ኣቡነ መቃርዮስ ሲመልሱ ፡
፩ኛ ግብፅና ኢትዮጵያ በእምነት ብቻ እንጂ በሌላ ኣንድ ኣይደሉም ብለዋል ፡፡
፪ኛ ይህን የተናገርከውን የሚለው በኣዋልድ መጻህፍት ስለሆነ የኣዳም ኃጢኣት ስንኳ ኣልደረሰብሽም የሚለውን የጻፉት ኣባ ሕርያቆስ ናቸው እንዲህ ዓይነቱን ኣንቀበለውም ብለው የቅዱሳኑን ቃል ኣቅለው የራሳቸውን ኣባባል ኣንጸባርቀዋል ፡፡
፫ኛ የምንነጋገረው በወንጌሉ ብቻ ነው ብለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የምታምንባቸውን ኣዋልድ መጻህፍትን በመልስ ኣነጋገራቸው ውድቅ ኣድርገዋቸዋል ፡፡
፬ኛ የደካማና ያልተማረ ኣነጋገር ነው ብለው ጥያቄ ያቀረቡትን ኣዛውንት ሽማግሌ በኣውደ ምሕረቱ ላይ ሆነው በሥልጣናቸው ተመክተው ተሳድበዋል ፡፡
፭ኛ እመቤታቺን የኣዳም ኃጢኣት ባይተላለፍባት ኣትሞትም ነበር ብለዋል ፡ በጥቅሉ የጳጳሱ ኣነጋገር ዘለፋንና ግሳጼን እንዲሁም ስድብን የተሞላ እንጂ የስብሰባን ስርዓት የተከተለ ባለመሆኑና ጠይቁ ብለው ፈቅደው ሲጠየቁ መልስ ባለመስጠት ሲሳደቡ ያዳመጡት ም እመናን ከባድ ቅሬታ ተሰምቷቸዋል ፡፡ ከኣንድ ጳጳስ የዚህ ዓይነት ኣነጋገር ቀርቶ ከተራ ቄስ የሚጠበቅ ኣይደለም ፡፡
በመሰረቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ታዋቂ ሊቃውንቶች ያሉዋትና ራሷን ችላ የምትስተዳደር እንጂ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጥገኛ ኣይደለችም ልትሆንም ኣትችልም ፡፡ስለሆነም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናት የሚነሳውን ውዝግብ ማየትና መወሰን የሚችለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ እንጂ የግብፅ ጳጳስ ኣይደሉም ፡ ከኣንድ የግል ቤተ ክርስቲያን ቢጻፍላቸውም ጣልቃ መግባት የለባቸውም ኣፈጻጸሙ ስርኣትን የተከተለ ኣይደለም ፡፡ የግብፅ ቤተክርስቲያንም ኣምስቱ እህት ኦርቶዶክስ ኣብያተ ክርስቲያናት በጋራ ስብሰባ በሚነጋገሩበት ጉዳይ የበኩሏን ሐሳብ የምትሰጥ እንጂ ጣልቃ የምትገባበት ምክንያት የለም፡፡
ሀ. ኣቡነ መቃርዮስ አዋልድ መጻህፍትን ኣንቀበልም በወንጌሉ ብቻ ነው የምናምነው በማለት በጥያቄው ተጠቅሶ የቀረበውን የቅዳሴውን መጽሀፍና መዝሙረ ዳዊቱንም ጭምር ኣልተቀበሏቸውም ማለት ነው ፡፡

ለ. እመቤታችን የኣዳም ኃጢኣት ባይተላለፍባት ኖሮ ኣትሞትም ነበር ላሉት የኣዳም ኃጢኣት ውርስ የሰው ዘር በሆነ ሁሉ መተላለፉ ኣይካድም ፡ እመቤታችንም ሰው ኣይደለችም ኣልተባለም ፡ ማደሪያው ኣድርጎ ስለፈጠራት ከህጻንነቷ ጀምሮ ኣንጽቷታል እንጂ ገብርኤል እስኪያበስራት ፲፭ ዓመት የኣዳምን ኃጢኣት ተሸክማ ኣልኖረችም ኣንጽቶ ቀድሷታል ለተባለው የሚቃወሙበት ኣስተማማኝ የሆነ ማስረጃ መስጠት ነበረባቸው ፡፡ ለመሆኑ በ፪ኛ ነገሥት ምዕራፍ ፪ ቁጥር ፲፩ ላይ ቅዱሱ ኤልያስ በኣውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ ይላል እንጂ ሞተ ኣይልም ፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ ፳፭ ቁጥር ፳፬ ላይ ደግሞ ሄኖክን እግዚአብሔር ወስዶታል ይላል እንጂ ሞተ ኣይልም ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በቅዱስ ቃሉ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ፲፮ ቁጥር ፳፰ ላይ ከነዚህ መካከል ሞትን የማይቀምሱ ኣሉ ብሏል ፡፡ ሌሎችም የመሳሰሉ ይገኛሉ ፡፡እነዚህ ሳይሞቱ የተሰወሩት ከላይ እንደተጠቀሰው እንደ ጳጳሱ ኣባባል የኣዳም ኃጢኣት ውርስ ኣልደረሰባቸውም ማለት ነውን ? ለሰሚ ግራ የሚያጋባ ነው ፡፡ በዚህ መልኩ ለእግዚኣብሔር የሚሳነው ነገር የለምና እመቤታችንን ከሕፃንነቷ ጀምሮ ኣንጽቷታል ቢባል ከእውነት የራቀ ነውን ?

ሐ. ኣዋልድ መጻሕፍትን ኣንቀበልም ካሉ በመጽሐፍ ቅዱሱ እመቤታችን ከየት እንደመጣች ስለማይገልጽ ከሰማይ ወረደች ሰው ኣይደለችም ሊባል ነውን ? በትክክል ከተመለከትነው የተዋሕዶን መሠረት የሚያፋልሰው እመቤታችን ከሰማይ ወረደች ሰው ኣይደለችም የሚባል ከሆነ ነው እንጂ እመቤታችንን እግዚኣብሔር ማደሪያው ልትሆን ስለመረጣት ከሕፃንነቷ ጀምሮ ኣንጽቶ ፈትሯታል ኃጢኣት የለባትም ንጽህት ነችማለት የተዋሕዶን መሠረት የሚያፋልስ ኣይደለም ፡ በመጽሐፍ ቅዱሱም በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፴፭ ላይ የተጠቀሰው ቅዱስ ገብርኤል ሲያበስራት ወንድ ሳላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል ስትለው መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል የልዑል ኃይልም ይፀልልሻል ካንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚኣብሔር ልጅ ይባላል በማለት ይጋርድሻል ይከልልሻል ይጠብቅሻል ብሎ ከሕፃንነቷ ጀምሮ ጠብቆና ኣንጽቶ እንዳቆያት ወደፊትም በዚያው መሠረት ጋርዶ እንደሚጠብቃት ገለጸላት እንጂ ከኣዳም ውርስ ኃጢኣት ያነጻሻል ኣላለም በዚህ ጊዜም ኣነፃት ተብሎ የተጻፈ ጽሁፍ የለም ፡፡ በኣጠቃላይ ንጽሕት ቅድስት መሆንዋን ስለሚገልጽ ለኣባባላቸው ማስረጃ ጠቅሰው በግልጽ ተንትነው ቢያስረዱ መልካም ነበር ፡፡

ጳጳሱ ኣቡነ መቃርዮስ ምንም ማስረጃ ጠቅሰው ሳያስተምሩ ለተጠየቀውም ጥያቄ መልስ ሳይሰጡ በዘለፋና በስድብ በግሳጼ ለማሳመን መሞከራቸው የሕዝብን መብት መድፈር ነውና እመቤታችን ከኃጢኣት ሁሉ የነፃች ቅድስት ናት ከማለት ሊያግዱ ኣይችሉም ፡፡ እሳቸው እንደእምነታቸው ባለንበት ዘመን ያሉት ሰዎች የጻፉትን እንጂ የእግዚኣብሔር መንፈስ እያናገራቸው ምንም ኃጢኣት ኣልደረሰባትም ያሉትን እንደነ ኣባ ሕርያቆስ ያሉትን ቅዱሳን ኣባቶቻቺንን ቃል ውድቅ ኣድርገው ኣልቀበልም ቢሉ መብታቸው ነው በዛሬይቱ ኃጢኣት በበዛበት ዓለም የምንገኘው ኃጢኣት ኣለባት ብንል ሐቀኛ የምንሆነው የትኛችን እንሆን ይሆን ? ቅዱሳን ኣባቶች ወይስ እኛ ? ይህን ጥያቄ ለተመልካች ትቼዋለሁ ፡፡
ሆኖም የተማረና ኣዋቂ ሰው ከሆነ የተማረውን ትምህርት በሚገባ በማስተማር ኣስተማማኝ የሆነ መልስ ይሰጣል እንጂ ጠይቁ ብሎ ሙሉ የጥያቄ መብት ከሰጡ በኋላ ለሚቀርበውጥያቄ ተገቢውን መልስና ማብራሪያ እንዲሁም የጥቅስ ማስረጃ መስጠት ሲገባ ጠያቂውን መዝለፍና መገሰጽ ብሎም የወንጌሉን ቃል ጥቅስ ጠቅሶ በኣሽሙር መሳደብ ከጳጳስ የሚጠበቅ ኣይደለም ኣንፈርድባቸውም ኣንድኣንድ ሰው ሥልጣኑን መከታ ኣድርጎ የእኔን ቃል ብቻ ለምን ኣሜን ብላችሁ ኣልተቀበላችሁም በማለት ወደ ዘለፋና ስድብ ያዘግማል ፡፡በኣጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዳክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናት የበላይ የሲናዶሱ ጉባዔ ስለሆነ እሳቸው በተግባር ኣንድ ኣይደለንም ኣዋልድ መጻሕፍትንም ኣንቀበልም እያሉ በዘለፋ በማስፈራራት ለማሳመን ያደረጉት ሙከራ ከትዝብት የሚጥላቸው ነው ፡፡
ምእመናን ሆይ ዲያብሎስ እግዚኣብሔርን ክዶ ለመላእክት ኣምላካችሁ ነኝ ባለበት ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል “ንቁም በበሕላዌነ እስከ ንረክቦ ለኣምላክነ” ኣምላካችንን እስክናውቅ በያለንበት ጸንተን እንቁም እንዳለው ሁሉ ቅዱሳን ኣባቶች በተጋደሉላት እምነት በመጽናት እስካሁን የምንከተለውን የቅዱሳናቹ ኣባቶቻቺንን መሠረተ እምነት ተከትለን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኣብያተ ክርስቲያናት እንደሚያምኑት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሕፃንነቷ ጀምሮ ቅድስት ንጽሕት ነች ምንም ኃጢኣት የለባትም የሚለውን ተመርኩዘን በእምነታችን መጽናቱ ሰላምን ይሰጠናል ፡፡
ውድ ኣባታችን ኣቡነ መቃርዮስ በጣም ይቅርታ ያድርጉልኝና ጥያቄ ኣቅርቡልኝ ብለው ፈቅደው ጥያቄ ሲቀርብልዎ በኣውደ ምሕረቱ ላይ ሆነው ጠያቂውን መዝለፍና መገሰጽ ብሎም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ጠቅሰው በኣሽሙር መሳደብ ከርስዎ የሚጠበቅና እግዚኣብሔ የሚወደው ኣድራጎት ኣይደለም ፡፡ እንዲያውም እርስዎ ስድብና ዘለፋ ለሚያስተላልፉ ሰዋች ኣርኣያ በመሆን ማስተማርና መገሰጽ ይገባዎታል እንጂ ከርስዎ እንዲህ ያለ ቃል ባልወጣም ነበር ፡ማንኛውም ሰው ክቡር ነው የከበረውን ሰው ማቃለል ኣግባብ ኣይደለም “ሸበቶ ጸጉርየክብር ዘውድ ነው” የሚለውን ማስታወስ ነበረብዎት ፡፡
ስድብና ዘለፋ የደረሰባቸው ኣባት ስድቡንና ግሳፄውን እንደ ኣባቶቻቸው በጸጋ በመቀበል ያለፉት ስልጣንዎን ኣክብረው እንጂ ኣፀፋውን ለመመለስና እንደ ስድብዎ ተናግረው ለማዋረድ ተስኗቸው ኣይደለም ፡፡ሐዋርያት የተፈጸመባቸውን ሥቃይና መከራ በጸጋ ተቀበሉት እንጂ ኣጸፋውን በመመለስበሰው ላይ ጥቃት ያደረሱበትና የተሳደቡበት ጊዜ የለም ፡፡ክርስቶስም በግፍ ስቃይ ኣድርሰውበት ለሰቀሉት “ኣባት ሆይ የሚያደርጉትን ኣያውቁትምና ይቅር በላቸው” ብሎ ለመነላቸው እንጂ ለድርጊቱ ኣጸፋውን ኣልመለሰላቸውም ፡ ቅድስ እስጢፋኖስም እንደዚሁ ፡፡
ኣባታችን እባክዎን ሌሎቹም ቢሆኑ ዘለፋንና የኣሽሙር ስድብን ሳይሆን በኣሽሙር ያልተሸፈነ ቅድስናን የሚያስተምር ጽሁፍ እንዲያስተላልፉ ቢመክሯቸው መልካም ነው ፡፡ ኣንዳንዶች በኢንተርኔት ጽሁፍ የስድብ መልእክት ሲያስተላልፉ መልስ ሳያገኙ የሚቀሩት የጤና መታወክ እንዳለባቸው ተቆጥረውና ስድብና ኣሽሙር መልስ የማይሰጠው ኣጸያፊ እግዚኣብሔር የማይወደው ኃጢኣት በመሆኑ ነው፡፡
ይህን ጽሁፍ ለማስተላለፍ የተነሳሳሁት ማንንም ለመጉዳትና ለመጥቀም ሳይሆን ብዕሬ ትክክለኛ የሆነውን እውነታ ሳትሰውር ለሕዝብ ጆሮ የማብቃት ልምድ ስላላት ነው ፡፡
ኣነሳስቶ ላጻፈኝ ለእግዚኣብሔር
ክብር ምስጋና ይግባው ኣሜን::
ከእዉነቱ ተከስተ

No comments:

Post a Comment